ድርጅቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ፣

  • በኢየሩሳሌም ለሚገኙ ገዳማትና መነኮሳት በየዓመቱ ስንቅ በማቅረብ፣ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ በመስጠት፣ በኢየሩሳሌም ደብረገነት ኪዳነምህረት ገዳማችን ግቢ ውስጥ ትልቅ ሠፊ አዳራሽና ማረፊያ ቤቶችን ሠርቶ ለምዕመናንና ለጳጳሳት ማረፊያ በበዓላት ወቅት መሰብሰቢና መመገቢያ ሆኖ እንዲያገለግል በማድረግ፣ በየዓመቱ ለትንሣኤ በዓል በኢየሩሳሌም ለሚገኙ መነኮሳት ለፆም መፈሰኪያ የሚውሉ ምግቦችንና ቁሳቁሶችን ከአዲስ አበባ እያጓጓዘ በማቅረብ፣ ይህንንም ተግባሩ ላለፉት 54 ዓመታት በተከታታይነት ሲያከናውን መቆየቱ፡፡ ቁጥራቸው ከ7 በላይ ለሚደርሱ የኢትዮጵያ ገዳማት አገልግሎት የሚውሉ ተሸከርካሪዎችን ገዝቶ በመስጠትና፣አገልግሎታቸውን ሲጨርሱም በመተካት፣ በየጊዜው የገንዘብ ዕርዳታ በመለገስ ለገዳማቱ ድጋፍ ሰጪና ለሚደርሱ ችግሮች ሁሉ ተቀዳሚና ተጠሪ በመሆን የገዳማቱ ህልውና እና የአገር ቅርስ ለመጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲሰጥና በመስጠት ላይ የሚገኝ አንጋፋ ተቋም ነው፡፡

በሀገር ውስጥ ያደረጋቸውን አስተዋጽኦ በተመለከተ፣

የአዲስ አበባ መስተዳድር የጎዳና ተዳዳሪ ታዳጊዎችን ለማቋቋም ለጀመረው ተግባር በቀዳሚነት የግማሽ ሚሊዮን ብር ድጋፍ በማድረግ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ በከፍተኛ ደረጃ እየተረባረቡበት ለሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የግማሽ ሚሊዮን ብር ቦንድ በመግዛትና ቦንዱ ጊዜው ሲያልቅም እንደገና በድጋሚ በዚሁ መጠን በመግዛት፣ በጦርነት ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ ቁጥራቸው ከአንድ ሺህ በላይ የሆኑ ሕጻናትን ተንከባክቦ በማሳደግና በማስተማር፣ በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት በረሀብ የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳትና ለማቋቋም ከመንግስት ጎን በመሆን በተለያየ ጊዜ የገንዘብ ዕርዳታ በመስጠት፣ለመንገድ ሥራና ሌሎች የመሠረት ልማት እንቅስቃሴዎች በተለያየ ጊዜ የገንዘብ እርዳታ በማበርከት፣በዕድሜ የገፉ አረጋውያንን በምግብ በአልባሳትና በመኖሪያ ቤት ጥገና በማገዝ፣ አያሌ የልማትና የበጎ አድራጎት ተግባራትን በማከናወን፤ ለቅርሶች እንክብካቤና ጥበቃ ድጋፍ በመስጠት፣በየዓመቱ ለትንሣኤ በዓል ወደኢየሩሳሌም ለሚያጓጉዛቸው ብዛት ያላቸው ምዕመናን የአየር ትኬት በመግዛት ከፍተኛ ገቢ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ እያስገባና ሌሎችንም ተመሳሳይ ተግባሮችን እያከናወነ የሚገኝ መሆኑ፣

ሌሎች ያስገኛቸው ጥቅሞችን በተመለከተ

 ድርጅታችን በየዓመቱ ከ300 የማያንሱ ምዕመናን ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም እየሄዱ ገዳሞቻቸውን ጎብኝተው መንፈሳዊ ተግባራቸውን ፈጽመው እንዲመለሱ እያደረገ መሆኑ፣የኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የሚገኙ ገዳማትንና መነኮሳትን ማገዝ ብቻ ሳይሆን የሀገራችን ንብረት የሆኑ ቅርሶችን በመጠበቅና በመንከባከብ ለሀገራችንና ለኅበረተሰቡ ተጨባጭና ጉልህ አስተዋጽኦ እየሰጠ የሚገኝ መሆኑ፣በተለይ በትንሣኤ ጊዜ እንደዛሬው ሌሎች አስጎብኝ ድርጅቶች ሳይበራከቱ በብቸኝነትና በፋና ወጊነት የሀገራችን ኢትዮጵያን ስም እያስጠራ ባህሏንና ወጓን እያሳወቀ ከመላው ዓለም ይመጡ ለነበሩት ኢትዮጵያውያን የበዓል ድምቀት ሰጪና መኩሪያ ተቋም ሆኖ መቆየቱና፡ በዚህም አፈፃፀሙ ቅርስ እንዲጠበቅ ድጋፍ ሲሰጥ የቆየ ብቻ ሳይሆን የባሕላችን አንፀባራቂ አምባሳደርም ሆኖ ሲሠራ የቆየ ተቋም ነው፡፡

 

የድርጅቱ የበላይ ጠባቂ

የድርጅቱ የበላይ ጠባቂ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሰ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ናቸው፡፡ የድርጅቱ የበላይ ጠባቂ፤ በጠቅላላ ጉበዔዉ የተመረጡት አባላት ለመተዋወቅ ሲቀርቡ አባታዊ ምክርን       ይሰጣሉ፡፡ በድርጀቱ ዉሰጥ ሰላምና ፍቅር የሚሰፍንበትን ሃይማኖታዊ ትምህርተ ይሰጣሉ፡፡ በማህበሩ አባላት ሃይማኖት ነክ የሆነ አለመግባባት ሲፈጠር መፍትሔ ይሰጣሉ፣ ወደ ቅደሰት ሀገር ኢየሩሳሌም ጉዞ በሚደረግበት ወቅት ከቅዱሰ ሲኖደስ አባላት ዉሰጥ ትምህርት፣ ምክርና ቡራኬ እየሰጡ የሚጓዙ አባት ይመድባሉ፡፡ ድርጅቱ ለሚያቀርበዉ ማንኛዉም ጥያቄ ድጋፍና ትብብር ይሰጣሉ፡፡