ሰው ዕለታዊ ፍላጎቱን ወይም ከዕለታዊ ፍላጎቱ በላይ ደስታ ቢደርግም በዚህ ዓለም የሚኖርበት ጊዜ አጭር ስለሆነች ሁሉም እንደ ጥላ ያልፋል፡፡
ይህ ዓለም የሥራ ዓለም ነው፡፡ በሚታየው በዚህ ዓለም ሥራ የማይታየውን ዓም እንደምንወርስ ቅዱሳት መጻሕፍት አስፋፍተው ያስተምሩናል፡፡ ሥራ በብዙ ዓይነት ይከፋፈላል፡፡ ለራስ ብቻ የሚሠራ አለ፡፡ ለብዙዎች ጥቅም ተብሎ የሚሠራ አለ፡፡ ከዚህ በቀር የራሱን የግል ፍላጎት በመከላከል ሀብታቸውንና ሕይወታቸውን ስለሌሎች መሥዋዕት የሚያደርጉ አሉ፡፡
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፈጠረው ፍጡር በበደለ ጊዜ ለፍጡሩ ሰው ሥርየተ ኃጢአት ለመስጠት ሲል ወደዚህ ዓለም መጥቶ ከኃጢአት በቀር መከራ ተቀብሎ የዓለም ቤዛነቱን በሞቱ ገልጧል፡፡ የጌታን ቤዛነት እያስታወሱ ከራሳቸው የግል ደስታ ይልቅ ስለ እግዚአብሔር ሰማያዊ ሀብት ብለው ምድራዊ ሀብታቸውንና አካላቸውን መሥዋዕት አድርገው ያቀረቡና የሚያቀርቡ ብዙዎች ናቸው፡፡
የሰው መንፈስ የዓለምን ፍጻሜ በሓሳቡ ውስጥ እያገናዘበ ለሚያልፈው ዓለም ከመጠበብ ይልቅ በሚያልፈው ደካማ ዓለም የማያልፈውን ዓለም ለመውረስ እንዲችል ነው፡፡
እምነትን መሠረት ያደረገ መንፈሳዊ አገልግሎት በብዙ ዓይነት ይከፋፍላል፡፡
ሀ. ከሀብት ቆርሶ በመስጠት፣
ለ. ወጥቶ ወርዶ በጉልበት ማገልገል፣
ሐ. በአሳብና በመንፈስ ፍጹም ሆኖ መገኘት፣
መ. ከልብ በመነጨ ኃዘንና ጸሎት ድርጊቱ እንዲቃና ማሰብ ነው፡፡
እነዚህ ሁሉ ተጠቃለው ከሥራ ላይ ሲውሉ ከታሰበው ግብ ይደርሳል፡፡ ይህንንና ይህንን የመሰለውን መሠረታዊ ሐሳብ በመከተል የኢትዮጵያ ምእመናን መታሰቢያ ድርጅት ለኢየሩሳሌም በሚል ስም ማኀበር ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
(ይህ ምክር አዘል ማስታወሻ በወቅቱ የቀረበው ድርጅቱን ያገለግሉ በነበሩ ታታሪ አባላት የተቋቋመው ይህ ድርጅት ብዙ ሥራ ስለሚጠይቅ ይበልጥ ለማጠናከር የተሰጠ ይሆናል)
በ1955 ዓ.ም ቅድስት አገር ኢየሩሳሌምን ለመሳለም ሄደው የነበሩት ኢትዮጵያውያን በአንድ ሐሳብና መንፈስ የድርጅቱን መቋቋምና አስፈላጊነት በመደገፍ በጉዳዩ መነሻ ቢሆንም መላው የኢትዮጵያ
ሕዝበ ክርስቲያን ይህንን መንፈሳዊ ድርጅት በፍጹም ልቡናው እንደሚደግፈው በማመን ነሐሴ 13 ቀን
1955 ዓ.ም ዓላማውን ለመደገፍና ለመተግበር ፍላጎት ላለው ኢትዮጵያዊ ክርስቲያን ሁሉ ሁኔታውን
አስታወቁ፡፡
በዚህ መሠረት አገር ወዳድና ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተቆርቋሪ የሆኑ
ምእምናን የድርጅቱን መቋቋም በሙሉ ልብ ስለደገፉትና በሥራም ስተባበሩ የካቲት 16 ቀን 1956 ዓ.ም የኢትዮጵያ ምእመናን መታሰቢያ ድርጅት ለኢየሩሳሌም በሚል ስያሜ ድርጅቱ ተቋቋመ፡፡