1994 ዓ.ም ሡልጣን በማስመልከት በጋዜጣ አንድ ማስታወቂያ ወጥቷል፡፡ ማስታወቂያው
የሚለው ኢየሩሳሌምን ለመሳለም ለደርሶ መልስ አራት መቶ ብር ብቻ ለዓየር መንገድ ቲኬት ወጭ በቂ በመሆኑን ገልጾ በዓለ ትንሣኤን ተሳላሚዎች በኢየሩሳሌም እንዲያከብሩ የሚያሳስብ ነበር በዚህ ማስታወቂያ መሰረት ከሠላሳ የማይበልጡ ኢትዮጵያውያን በግል ተነሣሥተው በማስታወቂያ የተገለጸውን ገንዘብ ከፈሉ፡፡
ሆኖም ኢየሩሳሌምን ለመሳለም ለተዘጋጁት ተጓዦች ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ ጉዞው ተሰረዘ፡፡ እነዚያው ተጓዦች እንደገና ተሰባስበው በ1995ዓ.ም ከኢትዮጵያ ዓየር መንገድ ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግ እያንደንዱ
ተጓዥ ብር 600.00 (ስድስት መቶ ብር) በመክፈል 1995ዓ.ም ቅዱሳት መካናትን ለመሳለም ወደ
ኢየሩሰሌም ሔዱ፡፡ ከመሔዳቸው በፊት ግን በኢየሩሳሌም ስለ አለው የኢትዮጵያውያን የታሪክ ይዞታና ሁኔታ የሚያውቅ ከሠላሳዎቹ ተሳላሚዎች አንድም ተጓዥ አልነበረም ከአገሩ ወደ አንድ ሌላ አገር የሚሔድ መንገደኛ ማድረግ የሚገባውን ዝግጅት ባለማድረጋቸው ተሳላሚዎ ከአዲስ አበባ ተነሥተው ኢየሩሳሌም አውሮብላን ጣቢያ ሲደርሱ የሚቀበላቸው አጥተው ችግር ስለ ደረሰባቸው ከቀኑ 9 ሰዓት እስከ 11 ሰዓት
ከአውሮፕላን ጣቢያ ሳይወጡ በመቆየታቸው ከባድ እንግልት ደርሶባቸዋል፡፡ በ11 ሰዓት የእንግዶቹ መጉላላት ያሳዘናቸው የአየር መንገዱ ሠራተኞች ከኢየሩሳሌም አውሮፕላን ጣቢያ ስልክ ደውለው ለዴር
ሡልጣን ገዳም 30 ኢትዮጵያን እንግዶች ከኢትዮጵያ መጥተው ተቀባይ ማጣታቸውን ተናገሩ፡፡
ከብዙ ዓመታት በኃላ ይህንን ያህል ብዛት ያላቸው ኢትዮጵያውያን በኢየሩሳሌም አደባባይ የታዩበት የመጀመሪያው ዓመት በመሆኑ የተሳላሚዎቹ ኢትዮጵያውያን መምጣት ሲሰማ የወገን ፍቅርና የአገር ናፍቆት ያጠቃቸው የገዳማቱ መነኩሳትና በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ እንግዶቹን ከሰማይ እንደ ወረዱ አድርገው ስለአሰቧቸው ማመን ተስኗቸዋል፡፡
ገዳማውያን አባቶች ወደ አውሮፕላን ጣቢያ በመሔድ ፈንታ ሆቴል በመፈለግ ደክመው ለእንግዶቹ ማሳረፊያ ሆቴል ስለ አጡ በየቤተሰቡ መካከል ሦስቱን፣ አራቱን፣ አምስቱን በመበታተን በምሪት ለማሳረፍ የሚያስችል ቦታ ሲያገኙ ወደ አውሮፕላን ጣቢያ መጥተው በደስታ ተቀበሏቸው፡፡

ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ገብተው እስከ አሥራ ሁለት ሰዓት ድረስ ከአውሮፕላን ጣቢያ ሳይወጡ የቆዩት እንግዶች የሔዱበት ወቅት የእስራኤላውያን አገር የክረምት መውጫ ጊዜ ስለ ነበረ የኢትዮጵያን አየር የለመደ ሰውነታቸው አልችል ብሎ ከብርዱና ከነፋሱ ኃይል የተነሣ ይንቀጠቀጡ እንደ ነበረ ተጓዦቹ ገልጸዋል፡፡
ሆኖም በመነኮሳቱ ጥረትና አስተባባሪነት ተሳላሚዎቹ በተለያዩ መንደሮች ውስጥ ማረፊያ ቦታ ማግኘት ችለዋል፡፡ ኢየሩሳሌም በገቡ ማግሥት በወገኖቻቸው መሪነት ቀራንዮንና ጎሎጎታን በአጠቃላይ ዴር ሡልጣንን የኢትዮጵያን የታሪክ ይዞታና በዚያ የሚገኙትን ቅዱሳት መካናት ተሳልመው ከጸሎተ ሐሙስ እስከ ትንሣኤ በዓል ያሉትን በዓላት በኢትዮጵያ ገዳም አሳልፈዋል፡፡ይህ ደግሞ እንግዶቹንስ የተቀበላቸው አበው መነኮሳት እነማን ነበሩ? የሚል ጥያቄን ያስጭራል፡፡ ከምድረ ኢትዮጵያ ድንገት ተነሥተው ወደ ኢየሩሰሌም
የሔዱትን ኢትዮጵያውያን ተሳላሚዎች የተቀበላቸው በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ቅዱሳት ገዳማትን በማገልገልና በመምራት ላይ የኖሩት፣ የመካናቱን ታሪክ ያጠኑና ችግርም በገዳማቱ ቦታዎች ላይ ሲከሠቱ በግንባር ቀደም በመከራከርና በእንግዳ ተቀባይነታቸው የታወቁት መጋቢ ገብረ ማርያም ኃይለ ማርያምና አባ ብርሃኔ ግርማ ጽዩን ናቸው፡፡
እነዚህ ሁለቱ አበው 1995 ተሳላሚዎቹን ከአውሮፕላን ጣቢያ ተቀብለው ማረፊያ በማፈላለግ ያስተናገዷቸው ሲሆን ቅዱሳት መካናትንም እያዞሩ የእያንዳንዱን ቦታ ታሪክ በማስረዳት ያስጎበኙአቸው
ናቸው፡፡ በማስጎብኘቱም ጊዜ የቀደሞ የኢትዮጵያ የታሪክ ይዞታዎች እንደ ተወሱ አስረድተዋቸዋል፡፡
ተሳላሚዎቹ ጉብኝታቸውን ከጨረሱ በኃላ በተደረገላቸው ገለጻ ላይ የኢትዮጵያ የታሪክ ይዞታዎች መወሰዳቸውን፣ ወገኖቻቸው ብቸኝነት እንደ ተሰማቸው፣ በተለይም በኢትዮጵያውን ገዳማትና በሌሎች አገራት ገዳማት መካከል ያለውን ልዩነት አትኩረው ስለ ተመለከቱ ልባቸው ተሰበረ፡፡
ኢትዮጵያውያኑ ተሳላሚዎች ያለፈው አልፏል፡፡ እኛም የጆሮ ሳይሆን የዓይን ምስክር ሆነናል፡፡ ወደፊት ምን ማድረግ እንደሚገባን ብትነግሩን? ብለው ሁለቱን አበው ጠይቋቸው፡፡
መጋቢ ገብረ ማርያም ኃይለ ማርያም እና አባ ብርሃኔ ግርማ ጽዩን ወደፊት ሊደረግ ስለሚገባው የሚከተለውን ሐሳብ እየተቀባበሉ ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡
የእኛ ኑሮ፡- የእኛ ኑሮ በዓይናችሁ ያያችሁት ስለ ሆነ ወደ ኃላ እናቆየውና እየተዘዋወርን ያሳየናችሁና
ያያችኋቸው የሌሎች አገራት የታሪክ ይዞታዎች አምረው፣ አሸብርቀውና ደምቀው የታዩት፣ ዜጎቻቸውም በጥሩ ሁኔታ ለመኖር የቻሉት በአገራቸው መንግሥት በተመደበላቸው በጀት ብቻ ሳይሆን ወገኖቻቸው በዓመት ሁለት ጊዜ ማለትም በበዓለ ልደትም በበዓለ ትንሣኤ እየመጡ ቅዱሳት ገዳማትን በሚጎበኙ ጊዜ በሚደርጉላቸው የገንዘብ ድጋፍን የመንፈስ ማበረታታት ነው፡፡
ማንኛውንም ሥራ ለመሥራት በእርግጥ ገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡ ሆኖም ለታሪክ ይዞታችን ክበርና ለእኛ የመንፈስ ጥንካሬ ከገንዘብ ይልቅ የበለጠ ዋጋ ያለው ቁጥራቸው የበዛ ወገኖቻችን በየዓመቱ እየመጡ በመካከላችን መገኘታቸውና መታየታቸው ነው፡፡
ከእኛ በፊት የነበሩት አባቶቻችን የኢትዮጵያን የታሪክ ይዞታ የዴር ሡልጣንን ገዳም ለማስከበር የመከራ ጽዋ እየጠጡ ሕይወታቸው አልፏል፡፡ አሁን ያልነውም ውሀና መብራት ሳይቀር ተነፍገን የሚደርስብንን ሥቃይ በፀጋ እየተቀበልን እነሆ አለን፡፡
የሞቱት አባቶቻችን ጾም ጩኸትና አሁን ያልነውም በአጠቃላይ ኀዘናችን ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶልናል መሰል ሠላሳ ቁጥር የደረሳችሁ ወገኖቻችን በመካከላችን በመገኘታችሁ እንደ አንድ ተአምርና ድንቅ ነገር እንቆጥረዋለን፡፡ ከዚህ የመጣችሁት ሠላሳ ብትሆኑም በአገሩ ሕዝብ ዘንድ (በምድረ እስራኤል)
የሚወራው ሦስት መቶ ኢትዮጵያውያን መጥተዋል እየተባለ ነው፡፡ ምናልባት ወደፊት የሚሆነው ታይቷቸው ይሆናል፡፡
ለእኛ ልታደርጉልን የሚገባው ኑሮዋችንን በዓይናችሁ አይታችኋል በዓይናችሁ በማየታቸሁ ለወደፊቱ ምን ማድረግ ይገባናል ብላችሁ እንደ ጠየቃችሁን እንዲሁም ሌሎች ወገኖቻችን እንደ እናንተ መጥተው ቢያዩን በአገር ፍቅር ስሜት እና በመንፈሳዊ ቅናት በመነሣሣት የሁላችሁም አመለካከት ተባብሮ ለታሪክ ይዞታችንና ለእኛም ለወገኖቻችሁ አለኝታ ትሆናለችሁ፡፡ ዛሬ ሠላሳ ሆናችሁ መጥታችኋል፡፡ አደራ የምንላችሁ ቢሆን ጨምራችሁ ባይሆን በዚሁ ቁጥር ልክ ባለማቋረጥ ብትመጡልን ለታሪካዊ ይዞታችንን ለእኛም ለወገኖቻችሁ ክብርና ሞገስ ታስገኙልናላችሁ፡፡
እኛ የኑሮ ችግሩን የለመድነው ስለሆነ እንተወው የአገርና የወገን ፍቅር አጥቅቶናል፡፡ የታሪክ ይዞታ ያላቸው ሌሎች የገዳማት መነኮሳት በየዓመቱ ለትንሣኤና ለልደት ወገኖቻቸው በመካከላቸው ሲገኙ ስለምይ

ሆደ ባሻ እየሆን እኛም አገርና ወገን ነበረን፣ ዳሩ ግን ብቸኛ የሆንበት ምክንያት ከቶ ምን ይሆን? አገርና ወገን እንደሌለን እየተቆጠርን ይሆን? ጥቃት የሚደርስብን ወገኖቻችን ከጎናችን ቆመው አይዝዋችሁ ቢሉን አንጠቃም ነበር፡፡ እያልን እርስበርሳችን እንነጋገራለን፡፡
እናንተን ደጋግመን የምናሳስባችሁ ለምእመናኑና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ችግራችንንና ብቸኝነት እንደተሰማን አብሥራችሁ ለሚመጣው ዓመት በብዛት እንድትመጡልን ነው ብለው ንግግራቸውን ደመደሙ፡፡
በማግስቱ የታሪክ ዕዳ የወደቀባቸው ተሳላሚዎች ወደ ዴር ሡልጣን ገዳም ገብተው ሳለ ታቦታቱ ያሉበትን ሁኔታ ሲያዩ የአርባ ዕቱ እንስሳና የቅዱ ሚካኤል አብያተ መቅደሲች በቁልፍ ተቆልፈው መተላለፊያ መንገድ ሲሆኑ አሥር ሰዎች እንኳን ማስቆም በማትችል ጠባብ ዋሻ ውስጥ ታቦተ ሕጉ ተቀምጦ የቅዳሴ ጸሎት የሚከናወነው በዚያች ጠባብ ዋሻ ውስጥ መሆኑን ለመገንዘብ ቻሉ፡፡ ከዋሻውም ጋር በማያያዝ በተወሰነ ካሬ ሜትር ስፋት ለትንሣኤ በዓል ማክበሪያ ድንኳን ተተክሎ ተመለከቱ፡፡ ከዚህ በኃላ ተሳላሚዎቹ ድንኳን መተከሉ ካልቀረ ለምን ሰፋ ተደርጎ እንዳልተተከለ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ መልሱ አሁን ድንኳን ከተተከለበት በላይ ስንዝር እልፍ ብለው በማስፋት መትከል እንደማይችሉ ከነምክንያቱ ተገለጸላቸው፡፡
በኢትዮጵያውያን ቅዱስና የታሪክ ይዞታ ነው፡፡ የተባለው ስፍራ ስፍራ ጸሎት በሚደረግበት ጊዜም ሆነ ገዳማውያኑ መነኮሳት በየግላቸው በሚኖሬባቸው ጎጆዎች ሻማ፣ ኩራዝና ጧፍ ይበራል፡፡ እንጂ የኤሌትሪክ መብራት አይበራም ወይም አልገባላቸውም፡፡ የልደት፣ የትንሣኤና የመሳሰሉት በዓላትም በሚከበሩብ ጊዜ መነኮሳቱ ማሾ ተከራይተው በማሾ ብርሃን ይገለገላሉ እንጂ የኤሌትሪክ መብራት የለም ነበር፡፡
ተሳላሚዎቱ ይህ አሳዛኝ ድርጊት መንፈሳቸውን ስለነካው ምክንያቱን በቅድሚያ ለማወቅ በአደረጉት ጥያቄ በኢትዮጵያ ቅዱስና የታሪክ ይዞታ ላይ የሚገኙት የአርባዕቱ እንስሳና የቅዱስ ሚካኤል አብያተ መቅደሶች የተዘጉበት ፣ መብራትና ውሀ የተከለከሉበት፣ ከተወሰነው ካሬ ሜትር በላይ አልፈው ድንኳን መትከል ያልቻሉበት ዋናው ምክንያት በግብፃውያን ኮፕቶች ተቃውሞና ተጽዕኖ መሆኑ ተነገራቸው፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ቅዱስና የታሪክ ይዞታ መግባት የሚቻለው በዋናው በር መሆን ሲገባ በኮፕቶቹ ተቃውሞና ተጽዕኖ መግባት ባለመቻሉ ቤት ፈርሶ በከፍተኛ ጥረት ትንሽ በር ስለተከፈተ ኢትዮጵያውያን የሚገቡበትና የሚወጡበት በዚያች ትንሽ በር መሆኑን ማየት ቻሉ፡፡
ከዚያው በር ጋር ተያይዞ የነበረውን የኢትዮጵያን ሰፊ የታሪክ ይዞታ ግብጻውያን ቀምተው በራሳቸው ቤተ ክርስቲያንና ትምህርት ቤት በመሥራት ከመጠቀማቸውም በላይ ተራፊውን የኢትዮጵያ ቅዱስ ስፍራ የራሳቸው ይዞታ በማስመሰል ለመስኮቦች መሸጣቸውን፣ የመስኮብ ገዳም የተሠራበትም የኢትዮጵያ ቅዱስ ቦታ መሆኑን ከአባቶች ተረዱ፡፡
ኢትዮጵያ በኢየሩሳሌም አፍሪካን ወክላ በቅድመ ታሪክ ገናና የነበረች ስትሆን አሁን ግን ታሪካዊ ይዞታዎችዋ ተወስደው በይዞታዋ ቁጥጥር ሥር ባለውም ቢሆን መብትዋን ተነፍጋ ባለ ታሪክ ያልነሩት ግብጻውያንና መሰሎቻቸው የኢትዮጵያን ታሪካዊ ይዞታ በመውሰድ ባለይዞታ መሆናቸው አልበቃቸው ብሎ አገሪቱ ያላትን ጨርሰው በመውሰድ ኢትዮጵያን ከቅዱስ ቦታ በማስወጣት ታሪክ አልባ ለማድረግ የግብጻውያን ጥረት አሁንም መቀጠሉን በተደረገላቸው ገለጻ ተገነዘቡ፡፡
እነዚያ እግዚአብሔር ለበጎ ሥራ የመረጣቸው ተሳላሚዎች ስለ ኢትዮጵያ የታሪክ ይዞታ በኢየሩሳሌም የሰሙትንና ያዩትን አገናዝበው አዘኑ በወገኖቻቸው ላይ የተደረገው ግፍና በደል ስለጨነቃቸው ወዲያው ኃዘናቸወንና ቁጭታቸውን ወደ ጎን በማቆየት፡-
 ምን እናድርግ  ? ካሉ በኃላ የታሪክ ይዞታችንን አክብረን እናስከብራለን የሚል ዓላማ አንግበው
ማድረግ የሚገባቸወን ሁሉ ለመፈጸም ቃል ተገባቡ ለዓላማቸውም ማስፈጸሚያ የሚሆኑ ዘዴዎችንም አፈላለጉ፡፡ ከዚህ በኃላ የሌሎች ክርስቲያኖችን አብያተ መቅደሶች የታሪክ ይዞታና የገዳማትን አጠባበቅ እየተዘዋወሩ መመልከትና ማጥናት ከዘዴዎቻቸው ፍለጋ አንዱ ሆነ፡፡ ስለዚህ ከሠላሳዎ ተሳላሚዎች አንዱ የነበሩት አቶ መኰንን ዘውዴ በፊት ቅድሚያ ሰጥተው የውጭ ሰዎች ገዳማትን እየዞሩ እንዲያጠኑ በጓደኞቻቸው ተመረጡ፡፡ የአቶ መኰንን ዘውዴ ጥናት፡-
የሌሎች ገዳማት የታሪክ ይዞታና አጠባበቅ፣ የመነኮሳቱም ኑሮ በከፍተኛ ደረጃ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ከእኛ ይዞታ ጋር እናነፃፅረው ብንል የሰማይና የመሬት ያህል የተራራቀ ይሆናል፡፡ ስለዚህ የሌሎችን የኑሮ ደረጃ አይቶ ማድነቅ ጠቃሚ አይሆንም፡፡ እነርሱ ከዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ የቻሉት እንደምን ባለ
ሁኔታና ከምን ከሚገኝ የገቢ ምንጭ እንደሆነ ለማወቅ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡ ከጥረቱም በተገኘው ውጤት ምንጩን ማወቅ ተችሏል፡፡ ምንጩ ከታወቀ ዘንድ  ምን ማድረግ አለብን  ? ብለው
በውይይታቸው ባነሡት ጥያቄ መሠረት ማድረግ የሚገባቸውብ ተገንዝበዋል፡፡